Membership Registration Form(አዲስ የማህበር አባላት መመዝገቢያ ቅጽ)

Invalid Input

Invalid Input

Invalid Input

Invalid Input/ User already exist

Invalid Input

I am not robot
Invalid Input

 

 ሀሁ ለሁሉም

የአማርኛ ቋንቋ የርቀት ትምህርት ቤት ማህበር

መተዳደሪያ ደንብ

 

“ ሀሁ ለሁሉም ” የቅዳሜ አማርኛ ቋንቋ ትምህርት ቤት በስዊዘርላንድ ሀገር የተመዘገበና በትርፍ ላይ ያልተመሰረተ ህጋዊ ሰውነት ያለው ማህበር ነው።

 

ይህ መተዳደሪያ ደንብ በማህበሩና በአባላቱ መካከል የሚጸና የውዴታ ግዴታ ውል ይሆናል።

 

ጥር 14. 2014 ዓ.ም / ጃንዋሪ 22. 2022

መግቢያ

 

ሀሁ ለሁሉም የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ቤት ማህበር በስዊዘርላንድ ፈቃደኛ በሆኑ ወላጆችና የማህበሩ ዓላማ ደጋፊ ግለሰቦች ዕድሜያቸው 5 ዓመትና ከዚያ በላይ ለሆኑ ህጻናትና ታዳጊዎች የአማርኛ ቋንቋ ፊደላትን እንዲለዩ፣ ጽሁፎችን እንዲያነቡና በቋንቋው መግባባት እንዲችሉ ለማስተማር የተቋቋመ ማህበር ነው።

የመማር ማስተማር ሂደቱ የሚካሄደው ተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርታቸው ነጻ በሚሆኑበት የሳምንቱ መጨረሻ ዘወትር ቅዳሜ ይሆናል።

ትምህርቱ በዋናነት አማርኛን በአፍ መፍቻ ቋንቋነት ለሚገለገሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚሰጥ ይሁን እንጂ፣ ከየትኛውም ባህል፣ ሃይማኖት፣ ሀገር ወይም አህጉር የሆነ/ችና ቋንቋውን የመማር ፍላጎት ያለው/ያላት መማር የምትችል/የሚችል ይሆናል።

ሀሁ ለሁሉም የአማርኛ ትምህርት ቤት ማህበር የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (UNESCO) እ.ኤ.አ በ 2004/2005 ባሳተመው ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ ባስቀመጠውና የሰዎች በተለይም የልጆች መደበኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት አስፈላጊነት በሚል ርዕስ ባሳተመው ቅጽ መርሆ ላይ በመመርኮዝ የተመሰረተ ሲሆን ይህንን ግብ ለማሳካትም በስዊዘርላንድ ሀገር ህጋዊ ሰውነት ኖሮት የሃገሪቱን የትምህርት ፖሊሲዎች፣ ህጎችንና ደንቦችን በማክበር የሚንቀሳቀስ ማህበር ነው።

  

አንቀጽ- 1

ዓላማ

 

ሀሁ ለሁሉም የአማርኛ ትምህርት ቤት ማህበር ደረጃውንና ጥራቱን የጠበቀ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት መስጠትን ዓላማው አድርጎ የተቋቋመ ሆኖ፣ ትምህርቱንም ችሎታና ብቃት ባላቸው መምህራን የሚሰጥ ይሆናል።

ተማሪዎች የአማርኛ ቋንቋን እንዲናገሩ፣ እንዲጽፉና መግባባት እንዲችሉ ለማድረግና የሀገራቸውን ወግ፣ ባህል እንዲሁም ታሪክና የመልክዐ-ምድር አቀማመጥ እንዲያውቁ የሚያስችል ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ማቅረብ ነው።

ማህበሩ ከላይ የተጠቀሱትን ዓላማዎቹን ለማሳካት በአጠቃላይ በመማር ማስተማሩ ሂደት ዙሪያ የወላጆችን የነቃ ተሳትፎ ያበረታታል።

በመሆኑም ወላጆች ልጆቻቸውን ለመማር ማስተማሩ ሂደት ዝግጁ እንዲሆኑ በማድረግ፤ የተሰጣቸውን የቤትና የክፍል ስራ በአግባቡና በሰዓቱ ሰርተው እንዲያስረክቡ በማገዝ፣ ከትምህርት ሰዓት ውጪ በቤት ውስጥም ይሁን በሌላ ቦታ ቋንቋውን እንዲናገሩ ማበረታታትና ከልጆቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ሁሉ ቋንቋውን በመጠቀም፣ በትምህርት ሰዓት እድሜያቸው ከ8 ዓመትና ከዚያ በታች የሆኑ ወይም በአማርኛ ቋንቋ መግባባት የማይችሉ ልጆች ወላጆች ከአጠገባቸው በመሆን በማገዝ፣ እንዳስፈላጊነቱ ማህበሩ በሚያዋቅራቸው ዋና ወይም ንዑሳን ክፍሎች በሚመደቡበት ጊዜ በፍላጎትና በንቃት በመሳተፍ እንዲሁም ስብሰባዎችን በመታደምና፣ ማህበሩ እገዛ በሚሻበት በማናቸውም ቦታና ጊዜ በፍላጎትና በንቃት በማገዝ ወላጆች የመማር ማስተማር ሂደት ዋነኛ አጋርና አንቀሳቃሽ እንዲሆኑ ያበረታታል።

 

አንቀጽ 2

የማህበሩ የስምና ተያያዥ የባለቤትነት መብት

ሀ.      የማህበሩን አርማ ወይም ማህተም ወይም ስም ለግል ጉዳይ ማዋል፣ ለሌላ ወገን አሳልፎ

መስጠት አጥብቆ የተከለከለ ነው።

ለ.      ከማህበሩ ምስረታ አስቀድሞ በ “ሀሁ ለሁሉም” ስም የተመዘገበ ህጋዊ ተቋም ከሌለ በስተቀር፣ የዚህ ስም የባለቤትነት መብት የ “ሀሁ ለሁሉም የአማርኛ ቋንቋ የርቀት ትምህርት ቤት ማህበር” ይሆናል።

አንቀጽ 3

የማህበሩ መቀመጫ

የማህበሩ መቀመጫ የሚሆነው፣ የማህበሩ ሰብሳቢ የሚኖርበት አድራሻ ይሆናል።

 

አንቀጽ 4

አባልነት

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ(ት)፣ ትውልደ-ኢትዮጵያዊ(ት) በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በጎሳ እንዲሁም ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መመዘኛዎች ልዩነት ሳይኖር በዚህ ት/ቤት ልጁን የሚያስተምር ወላጅ እንዲሁም ልጁ በዚህ ት/ቤት የሚማር ባይሆንም ለት/ቤቱ እድገት በሚደረገው እንቅስቃሴ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማድረግ ፈቃደኛና ዝግጁ የሆነ(ች) ግለሰብ አባል የመሆን መብቱ(ቷ) የተጠበቀ ነው።

 

4.1    የአባል መብት

ሀ.      የማህበሩን ዓላማና ራእይ የተቀበለ(ች) ለተግባራዊነቱም የበኩሉን(ሏን) ለመወጣት ዝግጁ የሆነ(ች)፤

ለ.      የማህበሩን ሕግና ደንብ አክብሮ(ራ) ለመንቀሳቀስ ዝግጁ የሆነ(ች)፤

ሐ.     የማህበሩን መዋጮ ለመክፈልና ሌሎች ግዴታዎችን ለመወጣት ፈቃደኛ የሆነ(ች) ማንኛውም

ኢትዮጵያዊ(ት) አባል መሆን ሲጠይቅ በአባልነት ይመዘገባል።

መ.     አባላት የማህበሩን አስተዳደር የመምረጥ እንዲሁም በማህበሩ የአስተዳደር እርከኖች ለመሳተፍ የመመረጥ መብት አላቸው። 

ሠ.     አባላት የማህበሩን የሂሳብ እንቅስቃሴ፣ የመማር ማስተማር ሂደቱንና የማህበሩን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የማወቅ መብት አላቸው።

ረ.      ቁጥራቸው 5 ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ አባላት የማህበሩን እንቅስቃሴ በተመለከተ አግባብ ያለው ጥያቄ ወይም አቤቱታ በደብዳቤ ካቀረቡ፣ የማህበሩ አስተዳደር አካላት ስብሰባ ጠርተው በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ መስጠት ወይም ከፊል (ሙሉ) ሪፖርት ማቅረብ አለባቸው።

ሰ.      1/4ኛው የማህበሩ አባላት ጥያቄ ካቀረቡ ልዩ ጠ/ጉባኤ እንዲጠራ ማድረግ ይችላሉ።

 

4.2    የአባልነት ግዴታ

ሀ.      የማህበሩን ዓላማና ራእይ ተግባራዊ ለማድረግ ገንቢ አስተዋጽኦ ማድረግ፤

ለ.      የማህበሩንና የት/ቤቱን ደንብና የስነ-ምግባር መመሪያዎች ማክበርና የማህበሩን አመራር

ውሳኔዎች ተግባራዊ ማድረግ፤

ሐ·     ማህበሩ በሚጠራቸው ስብሰባዎች ሁሉ መሳተፍ፣ በጋራ ሊሰሩ በታቀዱ እንቅስቃሴዎች መሳተፍ፤

መ·     የአባልነት መደበኛ መዋጮን በወቅቱ መክፈልና ሌሎች የገንዘብ መዋጮ ተግባራት ላይ

መሳተፍ፤

ሠ·     ከማህበሩ ሕግና ደንብ ውጪ የማህበሩን ዓላማ የሚፃረር ድርጊት ከመፈፀም መቆጠብ፤

ረ·      ለማህበሩ አላማና ራዕይ ታማኝ መሆንና ምስጢር መጠበቅ ናቸው።

 

4.3   አባልነት የሚቋረጥባቸው ሁኔታዎች

ሀ·      አንድ አባል በራሱ ፍላጎት አባልነቱ እንዲቋረጥ ጥያቄ ሲያቀርብ፤

ለ·      በሞት ሲለይ፤

ሐ·     በስነ ምግባር ጉዳዮች ለመወሰን ስልጣን ባለው አካል ከአባልነት እንዲታገድ ሲወሰን ነው።

 

አንቀጽ 5

የማህበሩ አወቃቀር

ማህበሩ ከላይ የተጠቀሱትን ዓላማዎቹን ያሳካ ዘንድ እንዲሁም የመማር ማስተማር ሂደቱን ቀልጣፋና የተሳለጠ እንዲሆን ከታች በዝርዝር የተመለከተውን አስተዳደራዊ መዋቅር ይከተላል።

 

5.1    ጠቅላላ ጉባኤ

ሀ.      ጠቅላላ ጉባኤው የማህበሩ ጠቅላላ አባላት ወይም ምልዐተ-ጉባኤ የሚባለው ሲሆን፣ የማህበሩ ከፍተኛ ወይም የመጨረሻው ወሳኝ አካል ነው።

ለ.      የማህበሩ ቋሚ አባሎች ሁሉ የጠቅላላ ጉባኤው አባላት ናቸው፤

ሐ.     ጉባኤው በማህበሩ ሰብሳቢ ወይም ም/ሰብሳቢ ይመራል፤

መ.     የጠቅላላ ጉባኤው ቃለ-ጉባኤ በሰብሳቢውና በዋና ጸሀፊው ይፈረማል፤

ሠ.     የማህበሩን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ይመርጣል፣ የስራ ክፍፍላቸውንም ያጸድቃል፤

ረ.      አስመራጭ ኮሚቴዎችን ይሰይማል፤

ሰ.      የዓመቱን በጀትና የስራ እቅድ ያጸድቃል፤

ሸ.      የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሚያቀርብለትን ዓመታዊ ወይም የመንፈቅ ዓመት የስራ ክንውን ሪፖርት መሰረት አድርጎ ይወያያል ብሎም ያጸድቃል፤

ቀ.      የአባላትን መዋጮ መጠንና የአከፋፈሉን ሁኔታ ይወስናል፤

በ.      የማህበሩን የመተዳዳሪያ ደንብ ያሻሽላል፤

ተ.      ማህበሩን ማፍረስ ይችላል።

  

አንቀጽ 6

ጠቅላላ ጉባኤ ስለመጥራት

ሀ.      የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ በአመት ሁለት ጊዜ ሲሆን፣ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው እንደአስፈላጊነቱ እያጠና ጠቅላላ ጉባኤ ሊጠራ ይችላል፤

ለ.      1/4ኛው ያህል የማህበሩ አባላት ጥያቄ ካቀረቡ ልዩ ጠቅላላ ጉባኤ መጥራት ይቻላል፤

ሐ.     እያንዳንዱ የጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊ ከስብሰባው ቀን በፊት ጥሪው እንዲደርሰው ይደረጋል፤

መ.     የስብሰባው አጀንዳዎች ከጥሪው ጋር አብረው ይላካሉ፤

ሠ.     ምልዐተ-ጉባኤ የሚባለው ከጠቅላላ ጉባኤ አባላት 50%+1 ያህሉ ሲገኙ ሲሆን፣ በዕለቱ በተገኙት አባላት የተወሰኑ ውሳኔዎች በምልዐተ-ጉባኤው እንደተወሰኑ ይቆጠራል፤

ሰ.      የጠ/ጉባኤ ስብሰባ ሁለት ጊዜ ያህል ተጠርቶ ምልዐተ-ጉባኤው ካልተሟላ፣ በሶስተኛው ጥሪ በተገኙት አባላት ምልዐተ-ጉባኤ እንደተሟላ ተቆጥሮ ጉባኤው ይካሄዳል። 

 

አንቀጽ 7

ድምጽ አሰጣጥ

ሀ.      በጠቅላላ ጉባኤ ላይ በአካል የተገኘ አባል አንድ ድምጽ ብቻ ይኖረዋል፤

ለ.      ውይይት የሚካሄደው ቀደም ብሎ በተዘጋጀው አጀንዳ ላይ ሲሆን፤ ተሰብሳቢው በዕለቱ አስፈላጊ

ናቸው ብሎ ያነሳቸው አጀንዳዎችም በድምጽ ብልጫ ካለፉ ሊካተቱበት ይችላል፤

ሐ.     ምርጫ በሚደረግበት ጊዜ የድምጽ አሰጣጥ በግልጽ ይካሄዳል፤

መ.     ጠቅላላ ጉባኤው በዕለቱ ስብሰባ ካለወጠው በስተቀር አጀንዳዎች ውሳኔ የሚሰጥባቸው እጅ በማውጣት ይሆናል፤

ሠ.     በአብዛኛው ድምጽ የተደገፈ ውሳኔ ተግባራዊ ይሆናል፤

  

አንቀጽ 8

የስራ አስፈጸሚ ኮሚቴ

ሀ.      በማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ በየሁለት አመቱ ይመረጣል።

ለ.      ሰብሳቢ፣ ም/ሰብሳቢ፣ ዋና ጸሃፊ፣ ገንዘብ ያዥ፣ ሂሳብ ሹም፣ የህዝብ ግንኙነት፣ ትምህርት አስተዳደር፣ የመረጃና ቴክኖሎጂ (ሙያዊ ስልጣኔ) አስተዳደርና የስነ-ምግባር ኮሚቴ አካላት ይኖሩታል፤

ሐ.     ማናቸውም የማህበሩ ወጪዎች በሰብሳቢው፣ በጸሃፊውና በሂሳብ ሹሙ ይፈረማሉ፣ ሰብሳቢው በሌለበት በምክትል ሰብሳቢው ይፈረማሉ፤

መ.     ማህበሩን በመወከል የሚደረጉ ግንኙነቶች ሁሉ በሰብሳቢውና በዋና ጸሃፊው ትብብር ይካሄዳሉ፤

ሠ.     ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች ሁሉ በቃለ ጉባኤ ይመዘገባሉ፤

ረ.      ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መመሪያዎችንና የዉስጥ ደንቦችን ያወጣል፤

ሰ.      የማህበሩን የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረትና ገንዘብ ያስተዳድራል፤

ሸ.      እንዳስፈላጊነቱ ንዑስ ኮሚቴዎችን ያቋቁማል፤

ቀ.      አንድ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ከለቀቀ በምርጫ ወቅት ተጠባባቂ/2ኛ ከፍተኛ ድምጽ ያገኘውን አባል መተካት ይችላል፤

በ.      አንድ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል በፈቃዱ ከመልቀቁ ከአንድ ወር በፊት ለስራ  አስፈጻሚ ኮሚቴው በጹሁፍ ማስታወቅ ይኖርበታል፤

ተ.      ትምርታዊ የውይይት መድረኮችን፣ ጉባኤዎችና ጉብኝቶችን ያዘጋጃል፤ እንዲሁም ለማህበሩ ገቢ የሚያስገኙ የተለያዩ ዝግጅቶችን ያጠናል፣ ያቅዳል ያዘጋጃል፤

ቸ.      አመታዊና ልዩ ጠቅላላ ጉባኤ እንዳስፈላጊነቱ ይጠራል፤

ኅ.      የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በወር አንድ ጊዜ በበይነ-መረብ ወይም በአካል በመገናኘት ስብሰባ የሚያደርግ ሲሆን፣ የስብሰባ አጀንዳዎች ቢያንስ ከስብሰባው 48 ሰዓት ቀድሞ ለስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ይላካሉ፣ ከአባላት በኩል ተጨማሪ አጀንዳዎች ካሉም በዕለቱ ቀርቦ በኮሚቴው አባላት ድጋፍ ካገኘ ለውይይት የሚቀርብ ይሆናል።

ነ.       የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው 50%+1 ያህሉ አባላት በስብሰባው ላይ ከተገኙ፣ ለመወሰን የሚያስችል ምልዐተ-ጉባኤ እንደተገኘ ይቆጠራል።

ኘ.      በስብሰባ ወቅት ሰብሳቢው ስብሰባውን ይመራል፣ ሰብሳቢው ካልተገኘ ም/ስብሳቢው ይመራል፣ ሁለቱም ካልተገኙ ጸሃፊው የመምራት ስልጣን ይኖረዋል።

አ.      ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የማህበሩን አጠቃላይ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች የሚያከናውን ሲሆን፣ ማናቸውም የገንዘብና ገንዘብ ነክ እንቅስቃሴዎች/ውሳኔዎች የኮሚቴው ምልዐተ-ጉባኤ ሳይሟላ ውሳኔ አይተላለፍባቸውም።   

 

አንቀጽ 9

ኦዲትና ቁጥጥር

ሀ.      ተጠሪነቱ ለጠቅላላ ጉባኤው ነው።

ለ.      በጠቅላላ ጉባኤው በየሁለት አመቱ ይመረጣል፤

ሐ.     የማህበሩን የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረትና ገንዘብ ይቆጣጠራል፤

መ.     የማህበሩን የሂሳብና ልዩ ልዩ ሰነዶች አስፈላጊ ሆኖ ባገኘው ወቅት ይመረምራል፤ የምርመራውን ውጤት ለጠቅላላው ጉባኤ ያቀርባል፤

 

አንቀጽ 10

ሰብሳቢ

ሀ.      የማህበሩን ጠቅላላ ጉባኤ እንዲሁም የስራ አስፈጻሚ ስብሰባዎችን ይመራል፣ የጠቅላላ ጉባኤ ቃለ ጉባኤ ላይ ከጸሃፊው ጋር በመሆን ይፈርማሉ፤

ለ.      ከማህበሩ የባንክ ሂሳብ ገንዘብ ወጪ ሲደረግ ከጸሃፊው እና ከሂሳብ ሹሙ ጋር በመሆን ይፈርማል፤

ሐ.     የማህበሩን ህገ ደንብ መሰረት በማድረግ፣ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማሳለጥ እንዲሁም ለማህበሩ የገቢ ማስገኛ የሚረዱ የተሻሉና ፈጠራ የታከለባቸውን ሃሳቦችን በማመንጨትና ከስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ጋር በመመካከርና አባላትን በማስተባበር ማህበሩን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ይተጋል።

 

አንቀጽ 11

ምክትል ሰብሳቢ

ሰብሳቢው በማይኖርበት ጊዜ የሰብሳቢውን ቦታ ተክቶ የሚሰራ ሲሆን፣ በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አቅራቢነት ሌሎች ሃላፊነቶችን በተደራቢነት ሊሰራ ይችላል።

 

አንቀጽ 12

ዋና ጸሃፊ

ሀ.      ለስብሰባ የተመረጡ አጀንዳዎችን ወይም በቀደመው ስብሰባ ውሳኔ ላይ ያልተደረሰባቸውን አጀንዳዎችን አዘጋጅቶ፣ ከስብሰባው ቀደም ብሎ ለስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት እንዲደርስ ያደርጋል።

ለ.      የጠቅላላ ጉባኤም ሆነ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባዎችን ቃለ ጉባኤ ይይዛል፣ ይሰንዳል፣ በጉባኤ/በስብሰባ የተገኙ አባላትን ይመዘግባል፣ ያስፈርማል።

ሐ.     የማህበሩን አጠቃላይ ቢሮ ነክ ስራዎችን፣ የጽህፈትና ጽህፈት ነክ ስራዎችን ያከናውናል።

መ.     ሰብሳቢውና ም/ሰብሳቢው በሌሉበት ስብሰባዎችን ይመራል።

 

አንቀጽ 13

ሂሳብ ሹም

ሀ.      የማህበሩን ገቢ፣ ወጪ እንዲሁም ወርሃዊና አመታዊ የሂሳብ ስራዎችን ያከናውናል፤

ለ.      የመንፈቅና አመታዊ የሂሳብ ሪፖርቶችን አዘጋጅቶ ለስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያቀርባል፤

ሐ.     የባንክና ሌሎች ተፈጻሚ የሚሆኑ ክፍያዎችን ከሰብሳቢው እና ከጸሃፊው ጋር በመሆን ይፈርማል።

 

አንቀጽ 14

ገንዘብ ያዥ

ሀ.      አጠቃላይ የማህበሩን ገንዘብ / ወርሃዊ ክፍያዎችን ጨምሮ/ ይሰበስባል፣

ለ.      ክፍያዎች መፈጸማቸውን ያረጋግጣል፤

ሐ.     የሂሳብ ሰነዶችን በአግባቡ ሰንዶ ያስቀምጣል፣ እንደአስፈላጊነቱ በሚጠየቅበት ጊዜ ያቀርባል። 

 

አንቀጽ 15

የመረጃና ቴክኖሎጂ (ሙያዊ ስልጣኔ) አስተዳደር

ሀ.      የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያግዙ የመገናኛ ዘዴዎችን ያመቻቻል፣ በየጊዜው የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ሂደቱን ያሳልጣል፤

ለ.      ከትምህርት አገልግሎት ጋር የተያያዙ የመገናኛ ዘዴዎች የቴክኒክ እክል ሲገጥማቸው፣ በተቻለ ፍጥነት ተስተካክለው አገልግሎቱ እንዳይስተጓጎል ይሰራል፤

ሐ.     ከትምህርት አስተዳደር ክፍል ጋር በመሆን፣ ለመማር ማስተማር ሂደቱ የሚያስፈልጉ ሰነዶችን፣ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችንና ዳታዎችን ያደራጃል፤

መ.     የማህበሩን ድረ-ገጽ፣ ማስተማሪያ ፕላትፎርሞችን/መተግበሪያዎችን እንዲሁም የመገናኛ ዘዴዎችን ይቆጣጠራል።

ሠ.     ከመረጃ ጋር የተያያዙ መመሪያዎችን ያወጣል።

 

አንቀጽ 16

የስነ-ምግባር ኮሚቴ

ሀ.      የማህበሩን እንቅስቃሴ እንዲሁም የመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ እክል የሚፈጥሩ፣ በአባላትም ሆነ በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መካከል የሚከሰቱ ችግሮችን ይመረምራል፣ ይሸመግላል፣ ውሳኔ ይሰጣል፣ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው ለጠቅላላ ጉባኤው ሪፖርት ያደርጋል፤

ለ.      የአባላትን ቅሬታ ይቀበላል፣ ይሸመግላል መፍትሄም ያፈላልጋል፣

ሐ.     የስነ-ምግባር እንከን ያለባቸውን መምህራንና፣ ተማሪዎችን ይመክራል፣ ያስጠነቅቃል፣ መክሮና አስጠንቅቆ ያልተመለሱ ካሉ ከሚመለከተው አካል ጋር ተነጋግሮ ውሳኔ ያሳልፋል። 

 

አንቀጽ 17

የትምህርት አስተዳደር

ሀ.      መምህራንን ያስተባብራል፤

ለ.      የመማር ማስተማሩ ሂደት በተገቢው ብቃትና ጥራት እየተካሄደ መሆኑን ይከታተላል፤

ሐ.     የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን ያዘጋጃል፣ ያደራጃል፤

መ.     በየደረጃው ላሉ ክፍሎች የሚመጥን ሥርዓተ-ትምህርት / Curriculum / ይቀርጻል፣ ያዘጋጃል፤   

ሠ.     ለትምህርት አሰጣጥ የሚያገለግሉ የበይነ-መረብ አገልግሎቶችንና፣ የድረ-ገጽ መተግበሪያዎችን ይቆጣጠራል፣ ያስተዳድራል።

ረ.      በስሩ የሚያስተባብራቸው የሥርዓተ-ትምህርት ንዑስ ክፍል፣ የወላጆች ን/ክፍል እና የመምህራን ን/ክፍሎች ይኖራሉ።

 

 17.1   የሥርዓተ ትምህርት ንዑስ ክፍል

በየደረጃው ላሉ ክፍሎች የሚመጥንና ደረጃውን የጠበቀ ሥርዓተ-ትምህርት / Curriculum / ይቀርጻል፣ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን ያደራጃል።

 

17.2   የወላጆች ን/ክፍል

ሀ.      በተማሪዎች፣ በወላጆችና በመምህራን መካከል የሚገጥሙ ችግሮችን ከትምህርት አስተዳደር ክፍል ጋር በመወያየት እንዲፈቱ ይጥራል፤

ለ.      ማህበሩ በሚያዘጋጃቸው የተለያዩ ዝግጅቶች ግንባር ቀደም ሆኖ ሃላፊነቱን በመውሰድ፣ ወላጆችን በማስተባበር ለዝግጅቶች ስኬት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል።

 

17.3   የመምህራን ን/ክፍል 

ሀ.      መምህራን ት/ቤቱ ባዘጋጀው ሥርዓተ-ትምህርት መሰረት ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ይሰጣሉ፤

ለ.       በየሴሚስተሩ መጨረሻ የተማሪውን ውጤት አዘጋጅተው ለትምህርት አስተዳደር ያቀርባሉ፤

ሐ.     ተማሪዎች በተገቢው መንገድ ትምህርታቸውን መከታተል አለመከታተላቸውን ይቆጣጠራሉ፣ ከአቅም በላይ የሆኑ ችግሮች ካሉም ለትምህርት አስተዳደር ሪፖርት ያቀርባሉ።

 

አንቀጽ 18

የህዝብ ግንኙነት

ሀ.      የማህበሩን ዓላማና ራዕይ ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ያስተዋውቃል፤

ለ.      የገጽታ ግንባታ ስራ ይሰራል፤

ሐ.     የማህበሩን እንቅስቃሴዎች በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን ማብራሪያና ቃለ-መጠይቆችን ያደርጋል።

 

አንቀጽ 19

የማህበሩ ጥሪት

ሀ.      ማህበሩ ከአባላቱ ከሚገኝ ወርሃዊ መዋጮና በተጨማሪም ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን በማካሄድ ገቢውን ያዳብራል፤ ከግለሰቦችና ከተመሳሳይ ደርጅቶች ስጦታና ድጋፍ ሊደረግለት ይችላል፤

ለ.      ማህበሩ ባለው ጥሪት(የገንዘብ አቅም) ብቻ እንቅስቃሴ ያካሂዳል።

 

አንቀጽ 20

ት/ቤቱን ስለማፍረስ

ሀ.      75% የሚሆኑ የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ አባላት በስብሰባው ላይ መገኘት አለባቸው፤

ለ.      3/4ኛው ወይም 75 ከመቶ የሚሆኑት አባላት እንዲፈርስ መስማማት አለባቸው፤

ሐ.     ት/ቤቱ ከፈረሰ ንብረቶቹ ተመሳሳይ አላማ ላላቸው ማህበራት ወይም ለበጎ አድራጎት ድርጅት ይሰጣል።

 

አንቀጽ 21

ይህን ደንብ ስለማሻሻል

ይህ ደንብ አስፈላጊ ተብለው የታመነባቸው ጉዳዮች ሲኖሩ ለማካተት ጠቅላላ ጉባኤው በሚሰይመው

የሕግ- አርቃቂ ኮሚቴ ተጠንቶ በጠቅላላ ጉባኤው ሲፀድቅ የሚሻሻል ይሆናል።

 

//////// ---////////   

Invalid Input