ሀሁ ለሁሉም የአማርኛ ቋንቋ የርቀት ትምህርት ቤት ማህበር

ሀሁ ለሁሉም የአማርኛ ትምህርት ቤት ማህበር በስዊዘርላንድ ፈቃደኛ በሆኑ ወላጆችና የማህበሩ ዓላማ ደጋፊ ግለሰቦች የተመሰረተ ሲሆን፣ ዕድሜያቸው 5 ዓመትና ከዚያ በላይ ለሆኑ ህጻናትና ታዳጊዎች የአማርኛ ቋንቋ ፊደላትን እንዲለዩ፣ ጽሁፎችን እንዲያነቡና በቋንቋው መግባባት እንዲችሉ ለማስተማር የተቋቋመ ማህበር ነው።

ትምህርቱ በዋናነት አማርኛን በአፍ መፍቻ ቋንቋነት ለሚገለገሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን የሚሰጥ ይሁን እንጂ፣ ከየትኛውም ባህል፣ ሃይማኖት፣ ሃገር ወይም አህጉር የሆኑና ቋንቋውን የመማር ፍላጎት ያላቸው ሁሉ መማር የሚችሉ  ይሆናል።

የመማር ማስተማር ሂደቱ የሚካሄደው ተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርታቸው ነጻ በሚሆኑበት የሳምንቱ መጨረሻ ዘወትር ቅዳሜ ነው።

ቋንቋ ሰዎች በዕለት ተዕለት ኑሮአቸዉ እርስ በርሳቸዉ መግባባት የሚችሉበት መሳሪያ ከመሆኑም በላይ የአንድን ማህበረሰብ ባህል፣ እዉቀት እና ፍላጎት አጠቃሎ የያዘ፣ እንዲሁም የአንድን ህብረተሰብ ምንነት እና ማንነት መግለጫ ነዉ።

ስለዚህ በተለያዩ ምክንያቶች ከህገር ውጪ የሚወለዱ እና የሚያድጉ ህጻናት ባህላቸዉን ማወቅና ቋንቋቸዉን መማር በጣም አስፈላጊያቸዉ ነዉ። ከዚህ ጋር ተያይዞም ህጻናት በለጋ እድሜያቸዉ በርካታ ቋንቋዎችን በቀላሉ መማር ስለሚችሉ እና በርካታ ቋንቋዎችን መማራቸዉ ለወደፊት የማህበራዊ ህይወታችዉ ጠቃሚ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።

ልጆች የትዉልድ ሰንሰለት እና የአገር መሰረት ተስፋዎች በመሆናቸዉ፣ በዉጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው ውጪ ተወልደው የሚያድጉ ህጻናትን ኢትዮጵያዊ ባህላቸውንና ቋንቋቸውን የማስተማር ሐላፊነትና የሞራል ግዴታ አለባቸዉ።


የቋንቋ ትምህርቱ አስፈላጊነት ልጆችን ከህጻንነታቸዉ ጀምሮ ስለአገራቸውና፣ ባህላቸዉ በሚገባቸዉ መልኩ የራሳቸው በሆነ ቋንቋ ለማስተማር ሲሆን፣ ልጆችን በብቃታቸዉና በእድሜያቸዉ ከፋፍሎ ደረጃዉን የጠበቀና ቀጣይነት ያለዉ ትምህርት መስጠት ይሆናል።

የትምህርቱ አላማ የህጻናቱን የእድሜና የቋንቋ ችሎታቸዉን ባገናዘበ መልኩ ስለታሪካቸዉና ባህላቸዉ በቂ እዉቀት እንዲኖራቸዉ ማድረግ ሲሆን፣ ልጆች አገራዊ እሴቶችን፣ በመረዳዳት፥ በትህትና፥ በመታዘዝና፥ በራስ በመተማመን ጎልብተው  እንዲያድጉ ማስተማር ነው።

 

አስተያየትዎን ይላኩልን This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ሀሁ ለሁሉም የአማርኛ ቋንቋ የርቀት ትምህርት ቤት ማህበር 

ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ

ስዊዘርላንድ